ይህ ፕሮጀክት ዲዛይኑን የሚመሩ የፍላጎቶች ስብስብ አለው። እነዚህ ፍላጎቶች WSDOT የትኞቹ ማሻሻያዎች አስፈላጊ እንደሆኑ — እና በኤጀንሲው እና በማህበረሰቡ አስተያየት ላይ ተመስርቶ የትኞቹ ተጨማሪ እድሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ — ለመለየት ይረዳሉ።
ሶስት አይነት ፍላጎቶች
WSDOT የፕሮጀክት ፍላጎቶችን በሶስት ምድቦች ይገልጻል:
- መሰረታዊ ፍላጎቶች: ፕሮጀክቱን የምንሰራበት ዋና ምክንያቶች ናቸው። የደህንነት፣ የስራ ማስኬጃ ወይም የህግ መስፈርቶችን ለማሟላት እነዚህ መታየት አለባቸው። እነሱም “እዚህ ለምንድነው ያለነው?” የሚለውን ጥያቄ ይመልሳሉ።
- የተሟሉ የመንገድ ፍላጎቶች: እነዚህ የእግረኞችን፣ የብስክሌት ነጂዎችን እና የህዝብ ማመላለሻ ተጠቃሚዎችን ጨምሮ ሁሉንም ተጠቃሚዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት የመንገድ ተደራሽነትን ለማቅረብ በህግ አውጪ መስፈርቶች የተገለጹ ናቸው። በተጨማሪም የመጓጓዣ መገልገያዎች ለሁሉም ሰዎች ምቹ እና ቀልጣፋ ወደ መድረሻዎች መድረስን ማስቻል አለባቸው።
- ዐውዳዊ ፍላጎቶች: እነዚህ በአካባቢው እና በማህበረሰቡ የተደገፉ ናቸው። በጀት፣ የጊዜ ሰሌዳ እና ከፕሮጀክቱ ግቦች ጋር መጣጣም ከቻሉ ሊታዩ ይችላሉ።
መሰረታዊ እና የተሟሉ የመንገድ ፍላጎቶች
- ደህንነት: ለሞት የሚዳርጉ እና ከባድ የአካል ጉዳት የሚያስከትሉ አደጋዎችን እንዲሁም እግረኞችን እና ብስክሌት ነጂዎችን የሚያካትቱ አደጋዎችን የመቀነስ ላይ ትኩረት ያደርጋል።
- ንቁ የመጓጓዣ መገልገያዎች: የWSDOT የተሟሉ የመንገድ መስፈርቶችን የሚያሟሉ እና ለእግረኞችና ለብስክሌት ነጂዎች የበለጠ ምቹ የሚያደርጉ ማሻሻያዎች።
- የሰፈር ትስስር: በአሁኑ ጊዜ በSR 900 የተከፋፈሉ የማህበረሰቡን ክፍሎች የሚያገናኙ ማሻሻያዎች።
- የትራንዚት ማሻሻያዎች: የህዝብ ትራንስፖርት ተደራሽነትን ለመጨመር እድል የሚሰጡ ማሻሻያዎች።
አሁን ያሉ ሁኔታዎች
- በእያንዳንዱ አቅጣጫ ሁለት መስመሮች ከግራ እና ቀኝ መታጠፊያ መስመሮች፣ እንዲሁም ከመንገድ ጠርዞች ጋር።
- የADA መስፈርቶችን የማያሟሉ የእግረኛ መወጣጫዎች።
- በSR 900 ላይ ባሉ ሁለት የትራፊክ መብራት መገናኛዎች ላይ ቁጥጥር የሚደረግባቸው መሻገሪያዎች አሉ፤ ነገር ግን በእግር፣ በብስክሌት ወይም በእጅ ጋሪ ለሚንቀሳቀሱ ሰዎች በቁጥጥር ስር ባሉ መሻገሪያዎች መካከል ያለው ርቀት ረጅም ነው።
- የWSDOT ደረጃዎችን የሚያሟሉ የእግረኞችና የብስክሌት ተጠቃሚዎች መገልገያዎች እጥረት።
ዐውዳዊ ፍላጎቶች
- ንቁ የትራንስፖርት የግል ደህንነት: እንደ መብራት ያሉ፣ ለእግረኞች ወይም ለብስክሌት ነጂዎች የግል ደህንነት ስሜትን የሚያሻሽሉ ባህሪያት።
- ውበት የሚያላብሱ ገጽታዎች: በማህበረሰቡ የሚመሩ ቦታዎችን ለመፍጠር እድሎችን መስጠት፣ ለምሳሌ በመንገዱ ላይ ምልክቶች ወይም የጥበብ ስራዎች።
- የትራፊክ ማረጋጋት: የተሽከርካሪዎችን ፍጥነት የሚቀንሱ ማሻሻያዎች።
- የወደፊት ተኳኋኝነት: የምዕራፍ ሀ ዲዛይን ከምዕራፍ ለ እና ሐ ጋር ያለው ተኳኋኝነት።